tg-me.com/orthodox1/13284
Last Update:
« ልደተ ስምዖን ነቢይ »
°°°°°°°°°ተ°°°°°°°°°°°°
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የካቲት ፰ ቀን ከሚከበሩ በዓላት መካከል የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ መግባት፣ የነቢዩ ስምዖን ልደት (መታደስ) እና የነቢዪት ሐና ዕረፍት በስፋት ይነገራል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን (ጥር ፮ ቀን) በኦሪቱ ሕግ መሠረት ሥርዓተ ግዝረትን ፈጽሟል፡፡ በተወለደ በዐርባኛ ቀኑ (የካቲት ፰ ቀን) ደግሞ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል፡፡ (ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት ከታኅሣሥ ፳፱ ቀን ጀምረን ስንቈጥር የካቲት ፰ ዐርባኛው ቀን ነው፡፡)
በቅዱስ ወንጌል እንደ ተመዘገበው ከሕርስ ደም የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ ‹‹የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ (የበኵር ልጅ) ዅሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ጠባቂዋ ጻድቁ ዮሴፍ ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሳትን ይዘው ጌታችንን በዚህች ዕለት ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ‹‹ከሕርስ ደም የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ›› ሲልም በሌሎች ሴቶች ልማድ ለመናገር ነው እንጂ በእመቤታችንስ ይህ ዅሉ ጣጣ የለባትም፡፡ ከሴቶች ተለይታ የተመረጠች ቅድስት የአምላክ እናት እንደ መኾኗ ለድንግል ማርያም ርስሐት በፍጹም አይስማማትም፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ከሕርስ ደም የሚነጹበት ጊዜ ሲደርስ›› ማለት ከሰው የሚለዩበትን ጊዜ ያመለክታል፡፡ ወንዶች በተወለዱ በዐርባ፣ ሴቶች በሰማንያ ቀናቸው ከሰው ይለያሉና፡፡
ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ በሔደ ጊዜም አረጋዊው ነቢዩ ስምዖን ታቅፎት ሰውነቱ ታድሷል፡፡ ይህ ዕለት (የካቲት ፰ ቀን) ‹‹ልደተ ስምዖን›› እየተባለ የሚጠራውም ዕለቱ ነቢዩ ጌታችንን ታቅፎ ከእርግናው (ሽምግልናው) የታደሰበት፤ ከደዌው የተፈወሰበት፤ አምላኩን በሥጋ ያየበት በአጠቃላይ ዳግም የተወለደበት ዕለት በመኾኑ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ስምዖን›› በሚለው ስም ከሚጠሩ ቅዱሳን መካከል ነቢዩ ስምዖን አንዱ ነው፡፡ የነቢዩን ታሪክ ለማስታዎስ ያህል አባታችን አዳም በተፈጠረ በአምስት ሺሕ ሁለት መቶ ዓመት በንጉሥ በጥሊሞስ ዘመነ መንግሥት የኦሪት መጻሕፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ እንዲተረጕሙ ከታዘዙ ሰብዓ ሰዎች (ሊቃናት) መካከል አንዱ ነቢዩ ስምዖን ነው፡፡
ይህ ነቢይ ትንቢተ ኢሳይያስ ደረሰውና እየተረጐመ ሳለ ‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፡፡ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች፤›› ከሚለው ኀይለ ቃል በደረሰ ጊዜ በቀጥታ ቢተረጕመው ንጉሡ እንደማይቀበለው በማሰቡ፤ እርሱም ‹‹ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› ብሎ በመጠራጠሩ ‹‹ድንግል›› የሚለውን ቃል ‹‹ወለት›› (ሴት ልጅ) ብሎ ተረጐመው፡፡ ተኝቶ በነቃ ጊዜም ‹‹ወለት›› የሚለው ቃል ተፍቆ ‹‹ድንግል›› ተብሎ ተጽፎ አገኘና እርሱም ‹‹ድንግል››ን ፍቆ ‹‹ወለት›› ብሎ ይጽፋል፡፡ ዳግመኛም ለሁለተኛና ጊዜ ተኝቶ ሲነቃ ቃሉ እንደ ነበረ ኾኖ ያገኘዋል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ቃሉን እፍቃለሁ ሲልም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ ‹‹የተጠራጠርኸውን፣ ከድንግል የሚወለደው ክርስቶስን እስከምታየውና እስከምትታቀፈው ድረስ ሞትን አትቀምስም፤›› ብሎታል፡፡
‹‹መሲሑን ሳታይ አትሞት›› የተባለው ነቢዩ ስምዖን አርጅቶ ከአልጋ ተጣብቆ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል ከኖረ በኋላ ትንቢቱ ተፈጽሞ፣ ዘመኑ ደርሶ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በዐርባኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ እስከ በገባበት ዕለት መንፈስ ቅዱስ አነሳሥቶ ወደ ምኵራብ ወሰደው፡፡ በዚያም ጌታችንን ከእመቤታችን ተቀብሎ ለመታቀፍ ታድሏል፡፡ ‹‹የምትጠብቀው ሕፃን ይህ ነው›› ብሎ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነገረው ጊዜም ታውረው የነበሩ ዓይኖቹ ተገልጠዋል፤ ሰውነቱም ታደሷል፡፡
ነቢዩም የእግዚአብሔርን ማዳን በዓይኑ በማየቱ፣ ከደዌው በመፈወሱ እና ከእርጅናው በመታደሱ በአጠቃላይ በተደረገለት ድንቅ ተአምር ዅሉ በመደሰቱ እግዚአብሔርን አመስግኗል፡፡ ‹‹አቤቱ ባሪያህን ዛሬ አሰናብተኝ፤ ዓይኖቼ ትድግናህን አይተዋልና፤›› በሚለው ትንቢታዊ መዝሙሩም ‹‹የእግዚአብሔርን ማዳን በዓይኔ ስላየሁ እንግዲህስ ልረፍ›› በማለት ሞቱን ተማጽኗል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም የክርስቶስን የዓለም ቤዛነትና ክርስቶስ በሥጋው በሚቀበለው መከራ እመቤታችን መራራ ኀዘን እንደሚደርስባት፤ እንደዚሁም ጌታችን ለሚያምኑበት ድኅነትን፣ ለሚክዱት ደግሞ ሞትን የሚያመጣ አምላክ እንደ ኾነ የሚያስገነዝብ ትንቢት ተናግሯል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ለነቢዩ ስምዖን የተደረገለትን ታላቅ ሥራ ሲያደንቁ እንዲህ ይገልጹታል፤ ‹‹ሰላም እብል እንዘ እዌድሶ ወእንዕዶ፤ መዝሙረ ማኅሌት በአስተዋድዶ፤ ክብረ ስምዖን ነቢይ ለክብረ ሱራፌል ዘይፈደፍዶ፤ እስመ ሐቀፈ መለኮተ ወገሠሠ ነዶ፤ እኤምኅ ሕፅኖ ወእስዕም እዶ፤ የማኅሌት መዝሙርን በማዘጋጀት እያከበርሁትና እያደነቅሁት ከሱራፌል ክብር ለሚበልጠው ለስምዖን ክብር ሰላም እላለሁ፡፡ እርሱ መለኮትን በእጁ ታቅፏል፤ እሳቱንም ዳሷልና እቅፎቹን እጅ እነሳለሁ፤ እጆቹንም እስማለሁ፤›› /መጽሐፈ ስንክሳር፣ የየካቲት ፰ ቀን አርኬ/፡፡ የዚህ አርኬ መልእክት ኪሩቤል፣ ሱራፌል (ሰማያውያን መላእክት) በእጃቸው የማይነኩት፣ ከግርማው የተነሣ የሚንቀጠቀጡለት፣ እሳተ መለኮቱ የሚቃጥል እግዚአብሔር ወልድን ነቢዩ ስምዖን በክንዱ ለመታቀፍ በመታደሉ ክብሩ ከመላእክት እንደሚበልጥ፤ ለክብሩም የጸጋ ምስጋና እና እጅ መንሻ ማቅረብ እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የነቢዪት ሐና ዕፍትም በዛሬው ዕለት ይታሰባል፡፡ ይህቺ ቅድስት ከአሴር ነገድ የተገኘች ደግ እናት ስትኾን አባቷም ፋኑኤል ይባላል፡፡ ክብረ ንጽሕናዋን ጠብቃ በድንግልና ኾና ዐሥራ አምስት ዓመት ሲሞላት ባል አግብታ ሰባት ዓመት ከባሏ ጋር ቆይታለች፡፡ ከባሏ ጋር ከተፋታች በኋላ ራሷን ጠብቃ ቀንም ሌትም ከምኵራብ ሳትወጣ በጾም በጸሎት ተወስና በሚቻላት ዅሉ እግዚአብሔርን እያገለገለች ሰማንያ አራት ዓመት ኖራለች፡፡ ይህቺ የአንድ መቶ ስድስት ዓመቷ አረጋዊት ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ በገባበት ዕለት በምኵራብ ተገኝታ አምላኳን በዓይኗ ለማየት በማታደሏ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት እና የዓለም ቤዛነት አመነች፡፡ ለዚህ ቀን ያደረሳትን እግዚአብሔርንም አመሰገነች፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታም የክርስቶስን ሥራ እያደነቀች የሰውን ድኅነት በተስፋ ለሚጠባበቁ ለኢየሩሳሌም ሕዝቦች አዳኝነቱን መሰከረች /ሉቃ.፪፥፴፮-፴፱/፡፡ በመጨረሻም በዛሬው ዕለት ዐርፋለች፡፡
ምንጭ፡-
መጽሐፈ ስንክሳር፣ የካቲት ፰ ቀን፡፡
የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ.፪፥፳፪-፴፱፡፡
ከዚህ ታሪክ ከምንገነዘባቸው በርካታ ቁም ነገሮች መካከል ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) አንዱ (ወልድ) ነው፡፡ እንደ አምላክነቱ በዅሉም ቦታ የመላ ነውና መሔድ መምጣት፣ መራብ መጠማት የባሕርዩ አይደለም፡፡ ስለዚህም ‹‹ሔደ፤ መጣ፤ ተራበ፤ ተጠማ፤ ተገረዘ፤ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ወዘተ.›› የመሳሰሉ ለፍጡራን የሚስማሙ ቃላት አይነገሩለትም፡፡ ነገር ግን መድኀኒታችን ክርስቶስ መገረዝ፣ መሔድ፣ መምጣት፣ መራብ፣ መጠማት የሚስማማው ሥጋን ለብሷልና የሰውነቱን ሥራ ይፈጽም ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ በተቀመጠው ሕግ መሠረት በተወለደ በስምንተኛው ቀን ለመገረዝ፤ በዐርባኛው ቀን ደግሞ ለመቀደስ
BY ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - 🇴🇷🇹🇭🇴🇩🇴🇽 🇹🇪🇼🇦🇭🇩🇴
Warning: Undefined variable $i in /var/www/tg-me/post.php on line 283
Share with your friend now:
tg-me.com/orthodox1/13284